የነዳጅ ውጤቶች ግብይት አዋጅ ወደ ትግበራ ሊገባ መሆኑ ተገለፀ።

 
በነዳጅ ሕገ-ወጥ ንግድ ላይ የሚሳተፉ አካላት ላይ እስራትን ጨምሮ ሌሎች ቅጣቶችን የሚጥለው የነዳጅ ውጤቶች ግብይት አዋጅ ወደ ትግበራ ሊገባ እንደሆነ በባለስልጣን መ/ቤቱ የህግ ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ ሃብታሙ ሚልኪ ገለጹ፡፡
በጥር ወር መጀመሪያ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ በአሁኑ ወቅት በነጋሪት ጋዜጣ ለመታተም በሂደት ላይ የሚገኘው አዲሱ አዋጅ በባለስልጣኑ ከተቀመጡ ሕጋዊ አሰራሮች ውጪ ነዳጅን በሚያከማቹ፣ በሚያጓጉዙ ፣በሕ-ገወጥ ንግድ የሚሳተፉ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አዋጁ የነዳጅ ውጤቶችን ከአስመጪ ጀምሮ ተጠቀሚው ጋር እስከሚደርስ ያሉ ሂደቶችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ መቆጣጠር የሚያስችሉ አሰራሮችን ያካተተና ቀልጣፋ፤ግልፅ፣አስተማማኝ፤ፍትሃዊ የአቅርቦትና ስርጭት አሰራርን የሚያጠናክር እንደሚሆን የገለጹ ሲሆን በተጨማሪም ነዳጅን መንግስት በተመነው ዋጋ ያለመሸጥ ችግሮችን ለማስተካከል ድርጊቱን በሚፈፅሙ አካላት ላይ አስተማሪ ቅጣት ተደንግጎበታል፡፡
 
በዚህም መሠረት ከመሸጫ ዋጋ በላይ በመሸጥ ለሚፈፀም የመጀመሪያ ጥፋት ከ350 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ በአዋጁ የተቀመጠ ሲሆን፤ ጥፋቱ በተደጋጋሚ ከተፈጸመ ከገንዘብ መቀጮ ተጨማሪ ከ3 እስከ 5 ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት እንደሚጣል ተመላክቷል፡፡ በተጨማሪም የነዳጅ ውጤቶችን ከተፈቀደው ቦታ ውጪ ያከማቸ፣ሊሸጥ ከሚገባው ሰው፣ቦታ እና የግብይት ሥርዓት ውጪ ሲሸጥ የተገኘ ማንኛውም አካል ከ3 እስከ 5 ዓመት በሚደርስ እስራት እና ከ300ሺህ እስከ 500ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ እንደሚቀጣ ተደንግጓል፡፡ እንዲሁም የነዳጅ ምርቶችን ሆን ብሎ ከባዕድ ነገሮች ጋር በመቀላቀል ለግብይት ማቅረብ ከ5 እስከ 7 ዓመት በሚደርስ እስራትና ከ350 እስከ 500 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ በአዋጁ ተቀምጧል፡፡
 
የነዳጅ ውጤቶችን ከተፈቀደለት የማጓጓዣ መስመር ውጪ ማጓጓዝ፣ከተፈቀደለት ማራገፊያ ስፍራ ውጪ ማራገፍ ወይም ወደ ጎረቤት ሀገር በኮንትሮባንድ ማጓጓዝ ከ5እስከ10 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከ400ሺህ እስከ 700ሺህ ብር እንደሚያስቀጣም ይጠቅሳል ብለዋል፡፡ እንዲሁም ከሚመለከተው አካል በጽሁፍ ፈቃድ ሳያገኝ የነዳጅ ውጤቶችን ነዳጅ ማደያ በሌለባቸው አከባቢዎች መሸጥ እስከ 5 ዓመት በሚደርስ እስራትና ከ300 እስከ 500 ሺህ ብር የሚያስቀጣ መሆኑ ተመላክቷል፡፡ 
 
በሌላ በኩል የባለስልጣኑ ወይም የሚመለከተውን አካል የቁጥጥር ሂደት መቃወም እና ማሰናከል ከአምስት ዓመት በማይበልጥ እስራትና ከ200 እስከ 500 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ በአዋጁ ተቀምጧል፡፡ በተጨማሪም የነዳጅ መቅጃ መሳሪያዎች የልኬት ሜትር ማስተካከያ ተደርጎበት በፕሎምፕ የታሠረውን መቁረጥ ወይም ልኬቱን ማዛባት ከ350 እስከ 500 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ በአዋጁ ተደንግጓል፡፡ ይህም አዋጅ በነጋሪት ጋዜጣ በይፋ ከታተመ በኋላ በቅርቡ ደትግበራ እንደሚገባ ስራ አስፈፃሚው አስተውቀዋል፡፡
 
  • Hits: 2358

Contact Us

Petroleum and Energy Authority 

P.O.BOX 2554

Tel +251 

FAX +251

Email pea.info@pea.gov.et

Addis Ababa

Ethiopia

Address

Addis Ababa Kadco Group building #2 From 7th to 8th floor. Ethio china Friendship Avenue around Wello sefere.