የኢነርጂ ቁጥጥር ስራዎችን ለማጠናከር በትብብር መስራት የሚያስችል ስምምነት ተደረገ
የኢነርጂ ቁጥጥር ስራዎችን ለማጠናከር በትብብር መስራት የሚያስችል ስምምነት ተደረገ
**********************************************************************************************************
የካቲት 24/2017 (ነ.ኢ.ባ)
በነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን፣ በጀርመን አለም ዓቀፍ ትብብር (GIZ) እና በኢትዮጵያ የጀርመን ኢነርጂ ትብብር (Ethiopian German Energy Cooperation Project ) መካከል የኢነርጂ የቁጥጥር ማዕቀፎችን ለማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት (MoU) ተፈረመ፡፡
ይህ የአጋርነት ስምምነት በኢነርጂ ዘርፍ የግል ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያስችል የኢነርጂ ቁጥጥር ስራዎችን ለማጠናከር የሚያስችሉ የህግ መዕቀፍ ዝግጅትን የሚደግፍ፣ በኢነርጂ ብቃትና ቁጠባ ስራዎች ላይ በትብብር ለመስራት እና በታዳሽ ኃይል ልማትን ለማሳደግ በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ ስምምነቶችን መሠረት ያደረገ ነው፡፡
የመግባቢያ ሰነዱ የተፈረመው ከሁለቱም ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች በተገኙበት ስነ ስርዓት ላይ ሲሆን ስምምነቱ የቁጥጥር ስራዎችን ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ ወሳኝ የሆኑ የቁጥጥር አሰራሮችን ለማሻሻል በሁለቱ ወገኖች የሚሰሩ የትብብር ስራዎችን ይዘረዝራል፡፡ ከፊርማ ስነ-ስርአቱ አስቀድሞ በስነ-ስርዓቱ ላይ ለታደሙ አካላት በኢትዮጵያ የጀርመን ኢነርጂ ትብብር ዳይሬክተር የሆኑት ሳምሶን ቶሎሳ ባደረጉት ገለፃ ከዚህ ቀደም ከባለስልጣን መ/ቤቱ ጋር በኢነርጂ ብቃትና ቁጠባ ፕሮግራሞች፣ በኤሌክትሪክ ተሸከርካሪ የህግ ምዕቀፍ ዝግጅት፣ በአነስተኛ ግሪድ ልማት ላይ ያተኮሩ የትብብር ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አውስተው እነዚህን እና ሌሎች ስራዎችን ጨምሮ በጋራ ለመስራት እና ግንኙነታችንን ለማጠናከር ይህ የጋራ መግባቢያ ስምምነት ግንኙነቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ያስችላል ብለዋል፡፡
የጀርመን አለምዓቀፍ ትብብር (GIZ) በኢትዮጵያ ምክትል ስራአስኪያጅ እና የአየር ንብረት ለውጥ ክላስተር አስተባባሪ ስቴቨን ሊሽባ ከፊሪማ ስነ-ስርዓቱ በኋለ ባደረጉት ንግግር የጀርመን መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በGIZ በኩል የሚሰራቸው ስራዎች እርዳታን ሳይሆን ትብብርን መሠረት ያደረጉና ዘላቂና አስተማማኝ የግንኙነት መሠረት ያላቸው ናቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሠሀርላ አብዱላሂ ባለፉት ሁለት ዓመታት በ GIZ ኢነርጂ ትብብር በኩል ባለስልጣኑ ለሚሰራቸው ስራዎች በተለይም በኢነርጂ ብቃትና ቁጠባ ስራዎች ላይ ከፍተኛ ድጋፍና ትብብር ሲደረግ መቆየቱን ገልጸው ይህ በሁለቱ ተቋማት መካከል የተደረገው የትብብር ስምምነትም ቀደም ሲል የነበረውን ትብብር ለማጽናት ያስችላል ብለዋል፡፡
|
- Hits: 2502