የነዳጅ ግብይት ረቂቅ አዋጅ መፅደቅ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ፡፡
የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ክህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ንግድና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በነዳጅ ግብይት ረቂቅ አዋጅ ላይ በዛሬው ዕለት ባደረጉት ውይይት፤ የረቂቅ አዋጁ መፅደቅ በነዳጅ ግብይት ላይ የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በውይይቱ ላይ በነበራቸው ቆይታ፤ በአዋጁ አስፈላጊነት እና ቀደም ሲል ይሰራበት የነበረው የነዳጅና የነዳጅ ውጤቶች አቅርቦት ሥራን ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ 838/2006 መተካት ያስፈለገበት ዋናኛ ምክንያት እና በአዋጁ ይዘት ላይ ማብራሪያ የጠየቁ ሲሆን በረቂቅ አዋጁ ይዘት ላይም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ባለስልጣን መ/ቤቱ ከአባላቱ በቀረቡለት ጥያቄዎች ላይ ሰፊ ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን በዋነኝነት ረቂቅ አዋጁን ማዘጋጀት ያስፈለገበት ምክንያት ቀደም ሲል በነበረው አዋጅ ያልተካተቱ ወሳኝ ጉዳዮች መኖራቸው፣ የቀደመው አዋጅ አቅርቦት ላይ ትኩረት የሚያደርግና ስርጭትን ግብይትን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ክፍተት ያለው መሆኑ፣ የቁጥጥር ስራውን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የተደረጉ የአሰራር ስልቶችን ያማያካትትና ወቅታዊ ባለመሆኑ እና በተለይ በግብይት ላይ የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥነት ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ መውሰድ ያማያስችል በመሆኑ ነው የሚል ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
በውይይቱ ማጠቃለያ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ አሻ ያህያ የአዋጁ ወቅታዊነት እና አስፈላጊነት በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ያማያጠያይቅ ጉዳይ መሆኑን ገልፀው ቋሚ ኮሚቴው ከባለስልጣን መ/ቤቱ ከተሰጠው ማብራሪያ በተጨማሪ በቀጣይ በትኩረት የሚመለከተው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
|
- Hits: 1106