በመዲናዋ ያለው የነዳጅ እጥረት ሰው ሰራሽ መሆኑ ተገለፀ።
በመዲናዋ ያለው የነዳጅ እጥረት ሰው ሰራሽ መሆኑን የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የነዳጅ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዲበራ ፉፋ ገልጸዋል፡፡ ኃላፊው በመዲናዋ አንዳንድ ማደያዎች ላይ የቤንዚን እና ናፍጣ እጥረት እንዳለ በማስመሰል በአቋራጭ ለመክበር ጥረት የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውን ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ጋር በቅንጅት በተደረገ ክትትል መረጋገጡን አስታውቀዋል፡፡
ባለስልጣኑ በመሰል ተግባራት ላይ የተሰማሩ አካላትን እንደማይታገስ እና ሕግ የማስከበር እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ እና ሸገር ከተሞች ጨለማን ተገን በማድረግ በሕገ-ወጥ መንገድ ነዳጅ የመጫን፣ የማዘዋወር፣ የነዳጅ መዳረሻን ወደ ኮንትሮባንድ አካባቢዎች የመቀየር ሕገ ወጥ ተግባራት መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም የነዳጅ መቅጃ ማሽኖች ላይ ወቅታዊ ጥገና ባለማስደረግ በነዳጅ አቅርቦት የመረጃ ሥርዓቱ ላይ የሚፈጠር እክል መኖሩን አንስተዋል፡፡
በወር ማገባደጃ የመጨረሻ ቀናት አካባቢው የነዳጅ ጭማሪ ይኖራል በሚል ነዳጅ የለም የማለት እና በካሽ የመገበያየት አሁንም ያልታረሙ ችግሮች እንደሚስተዋሉም ጠቁመዋል፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች ለማረም ከነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎች ጋር ውይይት መደረጉን ያነሱት አቶ ድበራ ፉፋ ፤ ከስህተታቸው በማይታረሙ ማደያዎች ላይ ሕግ የማስከበር እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ለአብነትም በሲዳማ ክልል በህገ ወጥ መልኩ ነዳጅ ከማደያ ውጭ እየሸጡ ስለመሆናቸው ጥቆማ በቀረበባቸው ማደያዎች ላይ ክትትል በማድረግ በዘጠኙ ላይ የአገልግሎት ፈቃድ የመንጠቅ እርምጃ መወሰዱን አመላክተዋል፡፡ ኃላፊው ነዳጅ ለመቅዳት በየቦታው የሚታየው ረጃጅም ሰልፍ በዜጎች ጊዜ እና ጉልበት ላይ የሚያደርሰውን ተጽእኖ ቀላል ባለመሆኑ ፤ ሰው ሰራሽ እጥረት በሚፈጥሩ አካላት ላይ ህብረተሰቡ የሚሰጠውን ጥቆማ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል፡፡
|
- Hits: 2213