የነዳጅ አከፋፋይ ኩባኒያዎች በስራቸው ከሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ጋር ውይይት በማድረግ ሪፖርት እንዲያቀርቡ አቅጣጫ ተሰጠ

 
ጥር 17 ቀን 2017 ዓ/ም

በነዳጅ ስርጭትና ግብይት ላይ በሚስተዋሉ ችግሮች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ውይይት ከነዳጅ አከፋፋይ ኩባኒያዎች ጋር የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በተገኙበት የተካሄደ ሲሆን በዚሁ መድረክ ሚንስትሩ በሰጡት አቅጣጫ ሁሉም ኩባኒያዎች ከሶስት እስከ አምስት ቀን ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በስራቸው ከሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ጋር በችግሩ ዙሪያ ተወያይተው ሪፖርት እንዲያደርጉ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

በሚንስትሩ ለተሰጠው አቅጣጫ መነሻ የሆነ ሪፖርት የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሠሀርላ አብዱላሂ  በነዳጅ ስርጭትና ግብይት ላይ የሚፈጸሙ ሕገ-ወጥ ተግባራትን ጥልቀትና ውስብስብነት በማሳረጃ የተደገፉ ማሳያዎችን ለኩባኒያዎች አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በማሳያነት ከቀረቡት ችግሮች መካከል በአብዛኛው ከአዲስ አበባና ሸገር ከተማ ጨለማን ተገን በማድረግ በሕገ-ወጥ መንገድ ነዳጅ የመጫን እና የማዘዋወር ተግባር ስለመኖሩ፤ ነዳጅ የተጫነለትን መዳረሻ በመቀየር ወደ ኮንትሮቦንድ አከባቢዎች ማጓጓዝ፣ የነዳጅ መቅጃ ማሽኖች ላይ ወቅታዊ ጥገና ባለመደረጉ የትክክለኝነት ችግር መታየቱ፤ በወር መዳራሻ ሳምንታት የነዳጅ ዋጋ ማሻሻያ ይደረጋል በሚል እሳቤ ሠውሰራሽ እጥረት መፍጠር፤ ከነዳጅ ግብይት ስርዓት ውጪ የካሽ ግብይት ማካሄድ፤የሚሉት በዋነኝነት የቀረቡ ሲሆን እነዚህ ተግባራት ሲፈፀሙ ኩባኒያዎች ተገቢውን ክትትል ያለማድረግ፣ የነዳጅ ማደያዎች ያሉበትን ደረጃ ተከታትሎ ጥገና ያለማድረግ እና በማደያዎች መካከል ፍትሃዊ የነዳጅ አቅርቦት ሂደትን አለመከተል የሚሉት ተነስተዋል፡፡

በመንግስት መዋቅርም ውስጥ በየደረጃው የሚገኙ አካላት ተገቢውን ቁጥጥር ባለማድረጋቸው፤ሕገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውርን እይቶ በዝምታ ማለፍ እና ከማደያ በታች ለሚቀርቡ የችርቻሮ ፈቃድ ከሕግ አግባብ ውጪ ሕገ-ወጥ ደብዳቤ መፃፍ ነዳጅ በጀሪካን እንዲቀዳ መፍቀድ፤ ለችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መሄድ የራሳቸውን ኃላፊነት እንደሚወስዱ በቀረበው ሪፖርት ላይ ተመላክቷል፡፡

የቀረበውን ሪፖርት ተከትሎ ሃሳባቸውን የገለፁ የኩባኒያ ኃላፊዎች የተገለጹት ችግሮች መኖራቸውን እንደሚቀበሉ ገልጸው ዘርፉ ብዙ ተዋኒያን የሚሳተፉበት በመሆኑ ቅንጅታዊ አሰራርና መናበብ እንደሚያስፈልግ በተጨማሪም ዘርፉን እየፈተኑ ያሉ የሎጂስቲክ ማነቆዎች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ሲሉ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የላይሰንሲንግና ሬጉላቶሪ ሚኒስትር ዲኤታ አብዱል ሀኪም ሙሉ (ዶ/ር) የጎላ የነዳጅ አቅርቦት ችግር በሌለበት የነዳጅ ዘርፉ እየተፈተነባቸው ያሉ ችግሮች ምንጭ ኮንትሮባንድና ሕገ-ወጥነት መሆኑን አፅኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ ችግሩ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ የመጣው የዘርፉ ተዋኒያን በአንድም በሌላም መልኩ ስለሚሳተፉበት ነው ያሉ ሲሆን ለዚህ ማሳያውም የነዳጅ አቅርቦት በኩባኒያዎች መርህ አልባ ግንኙነት በስራቸው ለሚገኙ ማደያዎች ፍትሃዊ አለመሆኑን በማሳያነት አንስተዋል፡፡

 

በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ በሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በተሰጠ አቅጣጫ ሁሉም ኩባኒያዎች በእኩልነት የሚታዩበት አሰራር መኖሩን ገልፀው በነዳጅ ግብይት ላይ የሚታዩት ችግሮች በዋነኝነት አለአግባብ ለመበልፀግ ከሚመነጭ ገፍላጎት ስለመሆኑ የቀረቡው ሪፖርት ላይ የታዩ ማስረጃዎች ጠቋሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በሕገ-ወጥነት ላይ እርምጃ ለመወሰድ ወደኋላ የማይባል መሆኑን በመረዳት ወደ አስገዳጅ እርምጃዎች ከመግባቱ አስቀድሞ ኩባኒያዎች በስራቸው ከሚገኙ ማደያዎች ጋር በመነጋገር ወደ-ሕጋዊ አሠራር እንዲመለሱ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ በመንግስት መዋቅር የሚገኙ አካላትን በተመለከተም ተመሳሳይ አቅጣጫ እንደተሰጠ ጨምረው ገልጸዋል::

 

Contact Us

Petroleum and Energy Authority 

P.O.BOX 2554

Tel +251 

FAX +251

Email pea.info@pea.gov.et

Addis Ababa

Ethiopia

Address

Addis Ababa Kadco Group building #2 From 7th to 8th floor. Ethio china Friendship Avenue around Wello sefere.