ባለፈው ሣምንት የአፍሪካ ርዕሰ መዲና በሆነችው የኛዋ አዲስ አበባ 2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ሲካሄድ ሰንብቷል፡፡

 

ባለፈው ሣምንት የአፍሪካ ርዕሰ መዲና በሆነችው የኛዋ አዲስ አበባ 2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ሲካሄድ ሰንብቷል፡፡ በዚህ ጉባኤ የባለስልጣን መ/ቤቱ ኢነርጂ ዘርፍ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ተሣታፊ የሆኑባቸው መድረኮች ተካሂደዋል፡፡

በነዚህ መድረኮች ውይይት ከተካሄደባቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል የኢነርጂ ተደራሽነት እና የመሠረተልማት ዝርጋታ በሚል ርዕስ በ children's investment fund foundation ፓቪሊዮን የተካሄደው ፓናል ውይይት አንዱ ነበር፡፡

በዚህ መድረክ ባለስልጣን መ/ቤቱን ወክለው አቶ ባህሩ ኦልጂራ የኤሌክትሪክ አቅርቦትና ሥርጭት ቁጥጥር መሪ ሥራ አስፈፃሚ በውይይቱ መክፈቻ ላይ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም በዋነኝነት በአህጉሪቱ ለአየርንብረት መበከል ከሚጠቀሱ ምክንያቶች አንዱ ከትራንስፖርት ዘርፉ የሚመነጭ በካይ ጋዝ ልቀት መሆኑን አንስተው አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት አማራጭ ብላ ለያዘችው ንፁህ፣አካታችና ዘላቂ የኢነርጂ ሽግግር አፋጣኝ መፍትሄ እንደሚያስፈልገው ጠቁመዋል፡፡

 ኢትዮጵያ ከምታመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል 95 በመቶ የታዳሽ ሃይል ምንጭ መሆኑን የሚጠቀስ ነው ያሉት አቶ ባህሩ አገሪቱ በትራንስፖርት ዘርፍ ብሔራዊ ኤሌክትሪክ ተሸከርካሪ ፕሮግራም ይፋ ማድረጓን ተከትሎ ኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች አገልግሎት ላይ እየዋሉ ከመሆኑ ጋር በተገናኘ ተሸከርካሪዎቹ ኃይል የሚሞሉት ኢትዮጵያ ከምታመነጨው ታዳሽ ሃይል የመነጨ ነው ብለዋል፡፡

የትራንስፖርት ዘርፉን በኤሌክትሪክ አማራጭ መቀየር ነዳጅን ከመተካት ያለፈ ጠቀሜታ አለው ያሉ ሲሆን ይህም ማለት በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሞሉ የተሸከርካሪ ባትሪዎች ኤሌክትሪክን የማካማቻ አማራጭ ተደርገው ሊወሰዱ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያም ለዚህ ምቹ መሠረተልማት እያዘጋጀች ትገኛለች ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ይህን ራዕይ ለማሣካት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እንደሚጠይቅ ገልጸው ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ ከፍተኛ የገበያ ዕድል ያላት መሆኑን አለምአቀፍና የአፍሪካ ባለሀብቶች እንዲያዩ ጋብዘዋል፡፡ ለዚህም እንደማሳያነት የአሁጉሪቱን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት የሰው ሃይል ያላት ከመሆኑ ባሻገር ንፁህና ታዳሽ በሆነ የኃይል ምንጭ የበለፀገችና ለዘርፉ ምቹ ፖሊሲ ያላት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ 

ፓናል ውይይቱም በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የቀጠናው ሀገራት ትብብር፣የፋይናንስ ማፈላላግ እና የግል ዘርፉ ሚና ሊያሳድጉ የሚችሉ የንግድ ሞዴሎች ማዘጋጀት ያላቸውን አስተዋዕጾ ትኩረት እንደሚያደርግ አንስተዋል፡፡ አያይዘውም አፍሪካ በዓለማችን እየተከሠተ ላላው ለአየርንብርት ቀውስ ምክንያት ባትሆንም የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማመንጨትና ለመወሰን ግን ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል፡፡

በንግግራቸው ማጠቃለያም የፓናሉ ተሣታፊዎች የአየር ንብረት ብክለትን ለመከላከል ኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ያላቸውን አቅም ለመጠቀም የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡